Tuesday, 18 September 2012

happy new year!!!

እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ በሰላም አሸጋገረን by eyasu etsub
እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ በሰላም አሸጋገረን እያልን መጪው ዘመን ካሳለፍናቸው ቅዱሳን አባቶች ታሪክ ብዙ የምንማርበት ያለብንን ደካማ ጎን
የምንፈትሽበት ሊሆን ያስፈልጋል፡፡ ያለፉት አባቶቻችን ብዙ ሥራ ሠርተው የብርሃን ችቦ አብርተው በክብር አስረክበውን አለፉ፡፡
ገና እነ ቅዱስ ጳውሎስ ክርስትናን ሳይቀላቀሉ አባታችን ባኮስ ክርስትናን ከሐዋርያት ተቀብሎ ወደ ሀገሩ ተመልሶ በማስተማር በዓለም የመጀመሪያው ተብሎ በታሪክ ላይ
ተመዝግቦ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ብርሃነ ወንጌልን በመቅረዝ ላይ ለኮሰ፡፡ በዚህም ትምህርቱ ቤተክርስቲያን በራሷ ሐዋርያ
ወንጌልን ተሰብካ በኢየሩሳሌም ላይ ጥምቀትን ፈጽማ የመጀመሪያው አድርጓት ለሌሎች ወንድሞች አስረከበ፡፡ እነ
ከሳቴ ብርሃን አባ ሰላማ፣ ዘጠኙ ቅዱሳን፣ ቅዱስ ያሬድ ሌሎችንም ጨምሮ ታላቅ ሥራን ሠርተው ለቀጣዩ ትውልድ
አስረከቡ፡፡ ክርስትና ሃይማኖትን ከምግባር ዶግማን ከቀኖና ታሪክን ከትውፊት ሥራን ከቅርጽ አስረክበውን የብርሃኑን ችቦ
ለኩሰው ብርሃንን ገልጠው አለፉ፡፡
የአክሱም አሻራዎች፣ የመርጦ ለማርያም፣ የተድባበ ማርያም፣ የጣና ቂርቆስና ሌሎቹም እጅግ ብዙ ቅርጾች አሁን ሕያው ሆነው የሚታዩንን ሁሉ አስረክበው ወደ ገነት
ታደሙ፡፡ አዲስ የሥነ ጽሑፍ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በያሬዳዊ ዜማ እግዚአብሔርን በዝማሜ በመርግድ በጽሕፋትና
በወረብ ማመስገንን /አቋቋምን/ አሁንም በእግዚአብሔር ጥበብ ተቀብለው ወደ ሚቀጥለው ዓለም ተሻገሩ፡፡ እነዚህ
ሁሉ አባቶቻችን ክርስትናን ተቀብለው ሲያስረክቡን በቀላሉና በተደላደለ ሁኔታ አልነበረም እሳት ዳር ሆነው ሳይሆን እሳት
ላይ ሆነው መከራን ተቀብለው ነው፡፡ እኛስ ዛሬ የዘመኑ አባቶች ካህናት ሰንበት ት/ቤቶች እና ምዕመናን ለመጪው ተውልድ ምን ለማስረከብ ተዘጋጅተናል? ዛሬ ከእኛ
ቤተክርስቲያን ብዙ ነገር ትጠብቃለች፡፡ ከኛም ዛሬ ከሚጠበቀው ነገር አንዱና ትልቁ ነገር በቤተክርስቲያን ዙሪያ ያለውን የፈተና እሳት ለማጥፋት ዳር ላይ ቆመን ሳይሆን እሳት
ውስጥ ቆመን እሳቱን ለማጥፋት ከእኛ ብዙ ይጠበቃል፡፡
ብንችል አዲስ ታሪክ ለመስራት ባንችል ደግሞ ያለውን ታሪክ ለማስጠበቅ ሁላችንም ባለን ጸጋ ቤተክርስቲያናችንን ለመጥቀም እና ልናገለግላት ቃል የምንገባበት ዘመን ሊሆን
ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ካህናት እና የሰበካ ጉባኤያት በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ መሆናቸው
ያሰብነውን ራዕይ ለማሳካት ይረዳናል፡፡ ስለሆነም መጪው ዘመን ዘመነ ማቴዎስ ለቤተክርስቲያን እንደቀደሙት አባቶች
መልካም አባት የምታገኝበት እኛም ልጆች ለቤተክርስቲያን የምንቆምላት ዘመን እንዲሆን ልንጸልይ ይገባል፡፡

No comments:

Post a Comment