Tuesday, 18 September 2012

፩. ነገረ ቅዱሳን /ክፍል አንድ/
መግቢያ
፩፡፩ ነገር ማለት፡- በቁሙ ሲተረጐም ቃል ፥ ንባብ ፥
ወሬ ፥ የቃል ፍሬ ፥ ከድምጽ ጋር የሚስማማ ፤
በጽሕፈት ፥ በአንደበት የሚገለጥ ፤ ከልብና ከአፍ
የሚወጣ ፥ በአንደበት የሚነገር ማለት ነው።
ይኸውም መንገርን ፥ መስበክን ፥ ማስተማርን ፥
ማውራትን ፥ ማብሠርን ፥ ነገርን ሳያቋርጡ እንደ
ውኃና ዝናም ማፍሰስን ፥ ማውረድን ፥
ማንጐድጐድን ፤ አሳብን ምሥጢርን በቃል
መግለጥን ፥ በንባብ ማስጌጥን ፤ መልክ እያወጡ ፥
ምሳሌ እየሰጡ ማነጽና መቅረጽን የሚያመለክት
ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ « ከጥንት
ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና
ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ፡፡ » በማለት
የዕብራውያን መልእክቱን የጀመረው ለዚህ ነው።
ዕብ ፩፡፩ ። ግዕዙ « በብዙኅ ነገር » ይለዋል፡፡
ቅዱስ ሚካኤልም ሙሴን፦ «እግዚአብሔር
አምላክ በስድስተኛው ቀን ፍጥረቱን ሁሉ ፈጥሮ
እንደጨረሰ የፍጥረትን ነገር ሁሉ ጻፍ፤ »
ብሎለታል፡፡ ግዕዙም የሚለው፦ « ጸሐፍ ኲሎ
ነገረ ፍጥረት፤ » ነው። ኲፋሌ ፪፥፬። በተጨማሪም
የሚከተሉትን ጥቅሶች እንመልከት።
- « ኢትኅፈር ነገረ ጌጋይከ ፤ የኃጢአትህን
ነገር መናገር አትፈር ፤ » ሢራ ፬ ፥ ፳፮
- « መኑ ይክል ነጊረ ምሕረቱ ጥንቁቀ ፤
የምሕረቱን ነገር ጠንቅቆ መናገር
የሚቻለው ማነው ? » ሢራ ፲፭ ፥ ፭
- « ዘአቅደመ ነጊረ በአፈ ነቢያት ፤
በነቢያት አፍ አስቀድሞ ያናገረው ፤ »
ሮሜ ፩ ፥፪
- « ለምንት ትነግር ሕግየ፤ ለምን አንተ
ሕጌን ትናገራለህ ? » መዝ ፵፱ ፥ ፲፭
- « ፈሪህየ ከመ እንግርክሙ ዘእኄሊ ፤
ዕውቀቴን የማስበውን እነግራችሁ ዘንድ
ፈርቼ ዝም አልሁ ፤ » ኢዮ ፴፪ ፥

፩፥፪ ፡- ቅዱስ ማለት በቁም ሲተረጐም ፦ የተቀደሰ ፥
ክቡር ፥ ምስጉን ፥ ልዩ ፥ ምርጥ ፥ ንጹሕ ፥ ጽሩይ
ማለት ነው። ለብዙ ሲሆን ቅዱሳን ይባላል።
በአጠቃላይ « ነገረ ቅዱሳን » የሚለው
ሲተረጐም፦ የቅዱሳንን ነገር መናገር ፥ መስበክ ፥
ማስተማር ፥ ማብሠር ፥ መጻፍ ይሆናል።
፪፡- ቅዱስ ማነው?
ከሁሉ በላይ ቅዱስ የሚባለው እግዚአብሔር
ነው። ጥንትም ፥ ዛሬም ፥ ለዘላለምም (ቅድመ ዓለም ፥
ማዕከለ ዓለም ፥ ድኅረ ዓለም) ቅዱስ ነው። በቅድስናም
የሚመስለው ማለትም የሚተካከለው የለም፡፡ ነቢዩ
አሳይያስ « እንግዲህ እተካከለው ዘንድ በማን
መሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ ፤ » በማለት የነገረን ይኽንን
ነው ። ኢሳ ፵ ፥ ፳፭ ፡፡
፪፥፩ ስሙ ቅዱስ ነው ፤
የእግዚአብሔር ስም ፍጡራን ከሚጠሩበት
ስሞች ሁሉ የተለየ ነው። ባሕርዩን ግብሩን የሚገልጥ
ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ « ከስም ሁሉ
የሚበልጥ ስም » ያለው ለዚህ ነው። « ወተወከልነ
በስሙ ቅዱስ በቅዱስ ስሙ ታምነናልና ፤» እንዲል ይህ
ስም መታመኛ ነው። መዝ ፴፪ ፥ ፳፩ ጠላቶቻችንን
የምንወጋው ፥ በላያችን ላይ የቆሙትን የምናዋርደው
በስሙ ነው። መዝ ፵፫ ፥፭። ቅዱስ ዳዊት፡- ንብ ማርን
እንደሚከብ የከበቡትን አሕዛብ ያሸነፋቸው ፥ በእሳት
እንደተያያዘ ደረቅ የእሾህ ክምር ያነደዳቸው ቅዱስ
በሆነው በእግዚአብሔር ስም ነው። መዝ ፩፻፲፯ ፥፲።
በጐልያድ ፊት በቆመ ጊዜም « አንተ ሰይፍና ጦር
ጭሬም ይዘህ ትመጣብኛለህ እኔ ግን ዛሬ
በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ በሠራዊት
ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ።» ብሎታል።
በጦር ተወግቶ ፥ በሰይፍ ተመትቶ ፥ በፈረስ በሰረገላ
ተገፍትሮ የማይወድቀውን ጐልያድን በእግዚአብሔር
ስም በጠጠር ጥሎታል። ፩ኛ ሳሙ ፲፯ ፥ ፵፭ ።
በአዲስ ኪዳንም ጌታችን አምላካችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስሙ አጋንንትን
እንደሚያወጡ ለደቀመዛሙርቱ ተናግሮላቸዋል። ማር
፲፮ ፥፲፯ ። ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ በቤተ
መቅደስ ደጅ ያገኙትን አንካስ በስሙ አርትተውታል።
የሐዋ ፫ ፥፮ ። አይሁድ በተደነቁ ጊዜም « በስሙም
በማመን ይህንን የምታዩትንና የምታውቁትን የእርሱ
ስም አጸናው ፤ » በማለት መስክረውላቸዋል። የሐዋ
፫፥፲፮ ። በኢዮጴ ጣቢታ ከሞት ልትነሣ የቻለችው
ቅዱስ ጴጥሮስ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለቀሰቀሳት
ነው። የሐዋ ፱፥፴። « ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም
በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ
የተመረጠ ዕቃ ነውና ፤ » በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ
የመሰከረለት ቅዱስ ጳውሎስም ጠንቋዩን በርያሱስን
በጌታ ስም ጨለማ አልብሶታል። የሐዋ ፲፫ ፥፲።
የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባትንም ሴት ፈውሷታል።
የሐዋ ፲፮ ፥፲፮ ።
፪፥፪ ባሕርዩ ቅዱስ ነው ፤
የእግዚአብሔር ባሕርይ ልዩ ነው። የባሕርይ
መገለጫዎቹም ብዙ ናቸው። እግዚአብሔር ፈጣሪ ፥ጌታ
፥ አምላክ ፥ ንጉሥ ነው ፤ ሁሉን የያዘ ሁሉን የጨበጠ
ነው፤ ሁሉን የጀመረ ሁሉን የጨረሰ ነው ፤ ከዓለም
አስቀድሞ የነበረ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ዘለዓለማዊ
ነው፤ የሚሳነው የሌለ ሁሉን ቻይ ነው ፤ ምሉዕ በኲላሄ
ነው ፤ ዐዋቂ ፥ ጥበበኛ ፥ ሕያው ፥ ኃያል ፥ ረቂቅ ፥
መሐሪና ቅዱስ ነው ፤ ፈታሒ በጽድቅ ኰናኒ በርትዕ ነው
፤ መፍቀሬ ሰብእ ነው ፤ መዓቱ የራቀ ምሕረቱ የበዛ
ትእግሥተኛ ነው ፤ መምህር ፥ ብርሃን ፥ አዳኝ ፥ መጋቢ ፥
ጠባቂ ፥ ረዳት ፥ ባዕለጸጋና አባት ነው።
ቅዱሳን መላእክት የባህርዩን ቅዱስነት
አውቀው፦ « ቅዱስ ፥ ቅዱስ ፥ ቅዱስ ፥ የሠራዊት ጌታ
እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች ፤ »
እያሉ በአንድነት በሦስትነት ያመሰግኑታል። ኢሳ ፮ ፥፫።
እሥራኤል ዘሥጋ ከባርነት ቤት የታደጋቸውን
እግዚአብሔርን ፦ « አቤቱ በአማልክት መካከል አንተን
የሚመስል ማነው? በምሥጋና የተፈራህ ፥ ድንቅንም
የምታደርግ ፥ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማነው ፤
» እያሉ ዘምረውለታል። ዘጸ ፲፭ ፥ ፲፮። ነቢዩ ኢሳይያስ
እግዚአብሔርን « የእስራኤል ቅዱስ » ብሎታል። ኢሳ
፭ ፥ ፲፮ ፣ ፵፯ ፥ ፬። በአጸደ ነፍስ ያሉ ሰማዕታትም፦ «
ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ ፥ እስከ መቼ ድረስ
አትፈርድም ፤ ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ
እስከመቼ አትበቀልም። » ሲሉ ተሰምተዋል ። ራእ
፮፥፱-፲፩ ።

No comments:

Post a Comment